ዶ/ር ቴድሮስ በደቡብ አፍሪካ ስለተገደሉ ኢትዮጵያዊያን የሰጡት አስተያየት የአገሪቱን ባለሥልጣናት አስቆጣ

ዶ/ር ቴድሮስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዶ/ር ቴድሮስ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በተገደሉ ኢትዮጵያዊያን እና ሞዛምቢካዊያን ዙሪያ የሰጡት አስተያት የአገሪቱ ባለሥልጣናትን አስቆጣ።

ዶክተር ቴድሮስ እሁድ ዕለት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ "ሌላ ዙር መጤ ጠል ጥቃት" እያገረሸ መሆኑን በመጥቀስ ድርጊቱ "አገሪቱ ለነጻነት ያደረገችውን ትግል የሚክድ አሳዛኝ" ሁኔታ ነው በማለት ገልጸውት ነበር።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር በደቡብ አፍሪካ ውስጥ በሚፈጸሙ መጤ ጠል ጥቃቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች መፈናቀላቸውን እና የሰው ሕይወት በአጭሩ እየተቀጨ መሆኑን በመግለጽ፣ በቅርቡ የሞቱ ኢትዮጵያዊያን እና ሞዛምቢካዊያንን በምሳሌነት ጠቅሰዋል።

በዚህም ቢያንስ አምስት ኢትዮጵያውያን እና አምስት ሞዛምቢካውያን መገደላቸውን ያመለከቱት የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ለሕይወታቸው በመስጋት እየሸሹ መሆናቸውን በኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

ይህንንም ተከትሎ የደቡብ አፍሪካ ባለሥልጣናት የዋና ዳይሬክተሩ አስተያየት ትክክል አለመሆኑን በመጥቀስ በአገሪቱ ውስጥ ተፈጥሯል ስለሚባለው መጤ ጠል ጥቃት ትክክለኛ እና አስተማማኝ መረጃን ለዓለም ጤና ድርጅት ለማስረዳት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።

ዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ትብብር መሥሪያ ቤት የሚባለው የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ዶክተር ቴድሮስ የጠቀሷቸው የውጭ ዜጎች ሕይወት በማለፉ እንደሚያዝኑ በመግለጽ ምክንያቱ ግን መጤ ጠል ጥቃት እንዳልሆነ አስተባብለዋል።

ባለሥልጣናት ለኢትዮጵያዊያኑ እና ለሞዛምቢካዊያኑ ሞት ምክንያቱ የመጤ ጠል ጥቃት አለመሆኑን ከመገልጻቸው በተጨማሪ፤ የኢትዮጵያዊያኑ ሞት ከተደራጀ ወንጀል ጋር እንደሚያያዝ፣ የሞዛምቢካዊያኑ ሞት ደግሞ ምርመራ እየተደረገበት እንደሆነ አሳውቀዋል።

ዶክተር ቴድሮስ በደቡብ አፍሪካ የነበረውን የአፓርታይድ ሥርዓት ለማፍረስ የአፍሪካ አገራት በጋራ መቆማቸውን በመግለጽ ኢትዮጵያ "ማንዴላን በመደገፍ ፓስፖርት ሰጥታ በአህጉሪቱ ውስጥ እንዲንቀሳቀሱ ስታደርግ፤ ሌሎች አገራትም እንዲሁ በተለያዩ መንገዶች ድጋፍ ማድረጋቸውን" አንስተዋል።

ነገር ግን አሁን በደቡብ አፍሪካ ውስጥ በአፍሪካውያን ስደተኞች ላይ እየተፈጸመ ያለው መጤ ጠል ጥቃት አገሪቱ "ለነጻነት ያደረገችውን ተጋድሎ የሚክድ ነው" በማለት ወቅሰዋል።

ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ ጨምረውም "አለመግባባቶች እና ቅሬታዎች በደቦ ጥቃት እና በጅምላ ጥቃት ሳይሆን በሕግ ሥርዓት እና በሕግ የበላይነት ብቻ ነው መፍትሄ ሊያገኙ የሚገባቸው" በማለት በስደተኞች ላይ የሚንጸባረቀው ጥላቻ እንዲቆም፣ ጥበቃ እንዲደረግላቸው እና ሰብአዊነት እንዲከበር ጥሪ አቅርበዋል።

ባለፉት ሳምንታት በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ፀረ አፍሪካውያን ስደተኞች ስሜቶች በይፋ እና በተዘዋዋሪ ሲንጸባረቁ ቆይተዋል። መንግሥት ሕጋዊ ያልሆኑ ስደተኞችን እንዲቆጣጠር የሚጠይቁ በርካታ የተቃውሞ ሰልፎች በመላዋ አገሪቱ ተካሂደዋል።

በተጨማሪም በውጭ ዜጎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን የሚያመለክቱ ዘገባዎች ሲወጡ ቆይተዋል። ነገር ግን ከእነዚህ ጥቃቶች ጋር በተያያዘ ዝርዝር መረጃዎች እና ቁጥሮች ከመንግሥት እስካሁን አልተሰጡም።

መንግሥት በሕገወጥ ስደተኞች ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን እና ዜጎች ሕግን በእጃቸው በማስገባት ምንም ዓይነት እርምጃን እንዳይወስዱ ሲያስጠነቅቅ ቆይቷል።

የዜጎቻቸው ደኅንነት ያሰጋቸው ጋናን እና ናይጄሪያን የመሳሰሉ አገራት ፍላጎቱ ያላቸውን ዜጎች ከደቡብ አፍሪካ ማስወጣት ጀምረዋል።